በበጎ ፈቃድ ተግባር የመረዳዳት ማህበራዊ እሴቶቻችንን በማጎልበት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ሲል የሞረትና ጅሩ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስታወቀ ።
በሰሜን ሸዋ ዞን የሞረትና ጅሩ ወረዳ ወጣት እና ስፖርት ጽ/ቤት በዘድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር ለማስጀመር ከእስትሪግ ኮሚቴው ጋር የባለፈው አመት የክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባር አፈጻጸም ግምገማ እና የዚህ አመት የክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባር እቅድና የተጀመሩ ተግባራትን ያሉበትን ቁመና ገምግሟል ።
መድረኩን የመሩት የሞረትና ጅሩ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ብዙሃን አሰፋ በዚህ አመት የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎበት በርካታ ተግባራቶችን አስተሳስረን የምንፈጽምበት ጊዜ ሊሆን ይገባል ብለዋል ።
የማንነታችን መገለጫ የሆነውን በጎ አስቦ ሰዋችን ማገዝና መርዳት የባህላችን እና የማንነታችን ማሳያ መስታውት በመሆኑ ዛሬም ነገም ወደፊትም ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ የተቀደሰ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል ።
አክለውም አቶ ብዙሃን የክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባር ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች በመለየት ሁሉንም ዜጋ በማሳተፍ በገንዘብ ፣ በጉልበት እና በሃሳብ በመረዳዳት ወገን ለወገን ትስስራችንን የምናጠብቅበት መሳሪያ ስለሆነ ሁሉም የስትሪንግ ኮሚቴ አባል እንደ ተቋም ያቀደውን ተግባር በርብርብ እንዲሰራ አሳስበዋል።